May 22, 2014 ነቢዩ ሲራክ
በለጋ እድሜዋ ትዳር መስርታ ሁለት ትጉህ መንታ ልጆች የታደለች እህት ከትዳር ጓደኛዋ ችግር ገጠማት። የ “ተበዳይ ነኝ!” ባይ ወዳጀን ምሬት ደጋግሜ ብሰማም ከቀናት በፊት “በደለኝ!” ያለችው የትዳር አጋሯ በኮሚኒቲው ሽምግልና ኮሚቴ በኩል ክስ መስራቱን እና የክስ ጥሪ እንደደረሳት ሰማሁ። ከአሰር አመት በፊት እድሜዋ ገና የ17 አመት እያለ የዛሬ የ12 አመት እድሜ የሆነውን ትልቁን ልጀን ያሳደገችውን እህት የቆየ አብሮነት ትውስታ እያሰብኩ የአለመግባባቱን ሽምግልና ወደሚከወንበት የጅዳ ኮሚኒቲ ሽምግልናውን ለመታዘብ መጓዝ ጀመርኩ። የያኔዋ ጉብል በኮንትራት ስራ መጥታ ከአሰሪወችዋ ልታመልጥ ከሶስተኛ ፎቅ የወደቀችበትን አሳዝኝ ታሪክ ጀምሮ ከብላቴና ልጀ ጋር ውለው ሲያድሩ የነበረውን ሁሉ ስደት እና ድህነት በልጅነት እድሜዋ ላይ የጣለውን ህመም አስታወስኩ። እግረ መንገዴን ይህን ሁሉ አውጥቸ አውርጀ ያ ሁሉ አልፎ ለዛሬ ወግ ማዕረግና ለመንታ ልጆች በረከት ያደላትን ፈጣሪ ስራ አስታውሸ” ለፈጣሪ ምን ይሳነዋል!” ስል አምላኬን አመሰገንኩት!
ወደ ኮሚኒቲው ጽ/ቤት ብዙም ሳልቆይ ደረስኩ። “በደል ደረሰብኝ!” ባይ ቀድማ በቀጠሮዋ ተገኝታለች ። “ልጆቸን ጥላ ሔደች” ባይ ከሳሽ ባል ዘግይቶ መጣ። ጉዳዩን ለመታዘብ ከባልም ለሚስትም ወገን የመጣን ታዛቢ ሽማግሌወች ሁለት ሶስት ስንሆን ሁላችንም በባልና ሚስት መካከል ሰላም እንዲወርድ ተመኘን። በበዳይ በተበዳይየደረሰወን ሁሉ የሚሰሙት ሽማግሌዎች መሆኑ በጀ። እኛ በበዳይ በተበዳይም ላይ ያረፈውን የዱላ አሸራ እያነሳን ብንሸመግል ሽምግልናው ፍርሻ በሆነ ነበር ስል ማሰቤ አልቀረም። ብቻ ኮሚኒቲው ከተመሰረተ በርካታ ጀምሮ በሽምግልናው ረገድ ተመሳሳይ ፋና ወጊ ማህበራዊ ጉዳዮችን በመስራት ላይ ያለው ኮሚቴ አባላት ትናንትም ዛሬም ቤት እንዳይፈርስ፣ ወገን ከወገኑ ሲጋጭ ገጭቱን በወግ በስርአት በማሸማገል ይሰራሉና ብዙውን አስታውሸ አመሰገንኳቸው። ትልቁን ስራ የሚሰራው የዚህ ኮሚቴ አባላት የዚህችን ብላቴና ትዳር ለልጆች ሲባል መታደጋቸውን ከበር ሆነን ሽምግልናውን ስንከታተል ለነበርነውን መልካም የምስራች አበሰሩን! ባልና ሚስት ልዩትን አስወግደው ለመኖር ተስማምተው ባንድ መኪና ተያይዘው ሲሔዱ የአብራካቸው ክፋዮችን ደስታ መመልከት በራሱ ልዩ የደስታ ስሜትን ይሰጥ ነበር)